ኦሪት ዘዳግም 32
Deuteronomy 32 · የ1954 አማርኛ · 53 ቁጥሮች
1ሰማያት ሆይ፥ አድምጡ፥ እኔም እናገራለሁ፤ ምድርም የአፌን ቃሎች ትስማ።
2ትምህርቴ እንደ ዝናብ ትፈስሳለች፥ ነገሬ እንደ ጠል ትንጠባጠባለች፤ በልምላሜ ላይ እንደ ጤዛ፥ በሣርም ላይ እንደ ካፊያ።
3የእግዚአብሔርን ስም እጠራለሁና፤ ለአምላካችን ታላቅነትን ስጡ።
4እርሱ አምላክ ነው፤ ሥራውም ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ የቀና ነው፤ የታመነ አምላክ፥ ክፋትም የሌለበት፥ እርሱ እውነተኛና ቅን ነው።
5እነርሱ ረከሱ፤ ልጆቹም አይደሉም፤ ነውርም አለባቸው፤ ጠማማና ገልበጥባጣ ትውልድ ናቸው።
6ደንቆሮ ብልሃተኛም ያልሆንህ ሕዝብ ሆይ፥ ለእግዚአብሔር ይህንን ትመልሳለህ? የገዛህ አባትህ አይደለምን? የፈጠረህና ያጸናህ እርሱ ነው።
7የዱሮውን ዘመን አስብ፥ የብዙ ትውልድንም ዓመታት አስተውል፤ አባትህን ጠይቅ፥ ያስታውቅህማል፤ ሽማግሌዎችህን ጠይቅ፥ ይነግሩህማል።
8ልዑል ለአሕዛብ ርስታቸውን ባወረሰ ጊዜ፥ የአዳምን ልጆች በለየ ጊዜ፥ እንደ እስራኤል ልጆች ቍጥር የአሕዛብን ድንበር አቆመ።
9የእግዚአብሔር እድል ፈንታ ሕዝቡ ነው፤ ያዕቆብም የርስቱ ገምድ ነው።
10በምድረ በዳ በጥማት፥ የነፋስ ጩኸትም በሞላበት ውድማ አገኘው፤ ከበበው ተጠነቀቀለትም፤ እንደ ዓይን ብሌን ጠበቀው።
11ንስር ጫጩቶቹን እንደሚያወጣ፥ በእነርሱም ላይ እንደሚሰፍፍ፥ ክንፎቹን ዘርግቶ ወሰዳቸው፥ በክንፎቹም አዘላቸው።
12እግዚአብሔር ብቻውን መራው፤ ከእርሱም ጋር ሌላ አምላክ አልነበረም።
13በምድር ከፍታ ላይ አወጣው፤ የእርሻውን ፍሬ በላ፤ ከዓለትም ድንጋይ በሚገኝ ማር፥ ከጭንጫውም ድንጋይ በሚገኝ ዘይት አጠባው፤
14የላሙንም ቅቤ፥ የመንጋውም ወተት፥ ከጠቦት ስብ ጋር፥ የባሳንንም አውራ በግ፥ ፍየሉንም፥ ከስንዴ እሸት ጋር በላህ፤ ከወይኑም ደም ያለውን ጠጅ ጠጣህ።
15ይሹሩን ወፈረ፥ ረገጠ፤ ወፈረ፥ ደነደነ፥ ሰባ፤ የፈጠረውንም እግዚአብሔርን ተወ፤ የመድኃኒቱንም አምላክ ናቀ።
16በሌሎች አማልክት አስቀኑት፥ በርኵሰታቸውም አስቈጡት።
17እግዚአብሔር ላልሆኑ አጋንንት፥ ለማያውቋቸውም አማልክት፥ በቅርብ ጊዜ ለተነሡ ለአዲሶች አባቶቻቸውም ላልፈሩአቸው አማልክት ሠዉ።
18የወለደህን አምላክ ተውህ፥ ያሳደገህን እግዚአብሔርን ረሳህ።
19ወንዶችና ሴቶች ልጆችም ስላስቈጡት እግዚአብሔር አይቶ ጣላቸው።
20እርሱም አለ። ፊቴን እሰውርባቸዋለሁ፤ ፍጻሜያቸው ምን እንደ ሆነ አያለሁ፤ ጠማማ ትውልድ፥ ያልታመኑም ልጆች ናቸው።
21አምላክ ባልሆነው አስቀኑኝ፤
22በዕብራይስጥ ይሹሩን የሚለውን ግዕዙ ያዕቆብ ይለዋል። በምናምንቴዎቻቸውም አስቈጡኝ፤ እኔም ሕዝብ ባልሆነው አስቀናቸዋለሁ፤ በማያስተውል ሕዝብ አስቈጣቸዋለሁ።
23እሳት ከቍጣዬ ትነድዳለችና፥ እስከ ሲኦል ድረስ ታቃጥላለች፥ ምድርንም ከፍሬዋ ጋር ትበላለች፥ የተራሮችን መሠረት ታነድዳለች።
24መከራን እጨምርባቸዋለሁ፤ በፍላጾቼም እወጋቸዋለሁ።
25በራብ በንዳድ ይጠፋሉ፤ በንዳድና በመራራ ጥፋት ያልቃሉ፤ የአራዊትን ጥርስ፥ የምድርንም እባብ መርዝ እሰድድባቸዋለሁ።
26ጕልማሳውን ከድንግል፥ ሕፃኑንም ከሽማግሌ ጋር፥ በሜዳ ሰይፍ፥ በቤትም ውስጥ ድንጋጤ ያጠፋቸዋል።
27እበትናቸዋለሁ አልሁ፤ ከሰዎችም መካከል መታሰቢያቸውን አጠፋለሁ።
28ነገር ግን ጠላቶቻቸው እንዳይታበዩ። እጃችን ከፍ ከፍ አለች እንጂ እግዚአብሔር ይህን ሁሉ አላደረገም ስለ ጠላቱ ቍጣ ፈራሁ።
29ምክር ያጡ ሕዝብ ናቸው፥ ማስተዋልም የላቸውም።
30አእምሮ ቢኖራቸው፥ ይህንን ያስተውሉ ነበር፥ ፍጻሜያቸውንም ያስቡ ነበር።
31እርሱ አምላካቸው ካልሸጣቸው፥ እግዚአብሔርም አሳልፎ ካልሰጣቸው፥ አንድ ሰው እንዴት ሺህን ያሳድድ ነበር? ሁለቱሳ እንዴት አሥሩን ሺህ ያሸሹ ነበር?
32አምላካችን እንደ አማልክቶቻቸው አይደለም፤ ጠላቶቻችንም ሰነፎች ናቸው።
33ወይናቸው ከሰዶም ወይን፥ ከገሞራም እርሻ ነው፤ ፍሬያቸው ሐሞት ነው፤ ዘለላውም መራራ ነው።
34የወይን ጠጃቸው የእባብ መርዝ፥ የእፉኝትም ሥራይ ነው።
35ይህ በእኔ ዘንድ ተጠብቆ የለምን? በመዝገቤስ የታተመ አይደለምን?
36የጥፋታቸው ቀን ቀርቦአልና፥ የሚመጣባቸውም ነገር ይፈጥናልና እግራቸው ሲሰናከል በቀልና ፍርድ የእኔ ነው።
37ኃይላቸውም እንደ ደከመ፥ የተዘጋ የተለቀቀም እንደሌለ ባየ ጊዜ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ይፈርዳል፥ ስለ ባሪያዎቹም ያዝናል።
38እርሱም ይላል። አማልክቶቻቸው የት ናቸው? ይታመኑባቸው የነበሩት አማልክት?
39የመሥዋዕታቸውን ስብ የበሉ፥ የመጠጥ ቍርባናቸውንም የወይን ጠጅ የጠጡ? እነርሱ ይነሡ፥ ይርዱአችሁም፥ መጠጊያም ይሁኑላችሁ።
40አሁንም እኔ ብቻዬን እኔ እንደ ሆንሁ፥ ከእኔም በቀር አምላክ እንደሌለ እዩ፤ እኔ እገድላለሁ፥ አድንማለሁ፤ እኔ እመታለሁ፥ እፈውስማለሁ፤ ከእጄም የሚያድን የለም።
41እጄን ወደ ሰማይ እዘረጋለሁና፥ እንዲህም እላለሁ። ለዘላለም እኔ ሕያው ነኝና
42የሚንቦገቦግ ሰይፌን እስለዋለሁ፥ እጄም ፍርድን ትይዛለች፥ ጠላቶቼንም እበቀላለሁ፥ ለሚጠሉኝም ፍዳቸውን እከፍላለሁ።
43ከተወጉት ከተማረኩትም ደም፥ ፍላጾቼን በደም አሰክራለሁ፤ ከጠላት አለቆችም ራስ ሰይፌ ሥጋ ይበላል።
44የባሪያዎቹን ደም ይበቀላልና፥ ጠላቶቹንም ይበቀላቸዋልና፥ ምድሪቱንና ሕዝቡን ይክሳልና እናንተ አሕዛብ ሆይ፥ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ።
45ሙሴም የነዌም ልጅ ኢያሱ የዚህችን መዝሙር ቃሎች ሁሉ በሕዝቡ ጆሮ ተናገሩ።
46ሙሴም ይህን ቃል ሁሉ ለእስራኤል ሁሉ ተናግሮ ፈጸመ።
47እርሱም እንዲህ አላቸው። የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ ይጠብቁና ያደርጉ ዘንድ ልጆቻችሁን እንድታዝዙበት ዛሬ የምመሰክርላችሁን ቃል ሁሉ በልባችሁ አኑሩት።
48ይህ ነገር ሕይወታችሁ ነው እንጂ ለእናንተ ከንቱ አይደለምና፤ በዚህም ነገር ትወርሱአት ዘንድ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ በምትገቡባት ምድር ረጅም ዘመን ትቀመጣላችሁ።
49በዚያም ቀን እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
50ወደዚህ በኢያሪኮ አንጻር በሞዓብ ምድር በዓባሪም ተራራ ውስጥ ወዳለው ወደ ናባው ተራራ ውጣ፥ ለእስራኤልም ልጆች ርስት አድርጌ የምሰጣቸውን የከነዓንን ምድር እይ፤
51ወንድምህም አሮን በሖር ተራራ እንደ ሞተ ወደ ወገኖቹም እንደ ተከማቸ፥ በወጣህበት ተራራ ሙት፥ ወደ ወገኖችህም ተከማች፤
52በእስራኤል ልጆች መካከል በጺን ምድረ በዳ በቃዴስ ባለው በመሪባ ውኃ ስለ በደላችሁኝ፥ በእስራኤልም ልጆች መካከል ስላልቀደሳችሁኝ፥
53ምድሪቱን ፊት ለፊት ታያለህ እንጂ ወደዚያች እኔ ለእስራኤል ልጆች ወደምሰጣቸው ምድር አትገባም።

